አማርኛ

መግቢያ

ዛሬ የምንኖርባት ዓለም ዓመፅ፣ ትርምስ፣ ተስፋ መቁረጥና ውስጣዊ ብቸኝነት እየጨመሩባት ያሉባት ዓለም ናት።  በዚህች ዓለም እጅግ ብዙ ሰዎች እንደ ዕለታዊ የዜና ዋና ዋና ርዕሶችና ማኅበራዊ ሚዲያ ባሉ ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች እርስ በርሳቸው ይገናኛሉ።  በዚህም ምክንያት፣ ብዙ ሰዎች በየዕለቱ ስለሚጋፈጧቸው ቁጥር የሌላቸው ችግሮችና አሳዛኝ ክስተቶች ያለን ግንዛቤ እየጨመረ ነው።  እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ለብዙ ሰዎች የማያቋርጥ ጉጉት፣ እርካታ፣ እንዲያውም አእምሮን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር መጠመድ ምንጭ እየሆኑ ነው።

በዓለማችን ያሉ ቀልብ የሚስቡ አስደንጋጭ ችግሮች ያለማቋረጥ ስለሚደርሱን፣ በየቀኑ በኃጢአት የወደቀው ዓለም ወደሚታይበት አሳዛኝ ሁኔታ እንሳባለን። በተመለከትንበት ቦታ ሁሉ ኃጢአትንና ውጤቶቹን እናያለን፤ ይህም ነፍሳችንን ይጎዳል።

ታዲያ የብዙ ሰዎችን ክፋት፣ ኃጢአትና ሥቃይ እንዲህ በተደጋጋሚ እያወቅን መኖራችንን እንዴት እንጋፈጠው? ለዚህ ብቸኛው መልስ የዚህ መጽሐፍ ዋና ጉዳይ የሆነው የእግዚአብሔር ምሕረት ነው።

የእግዚአብሔር ምሕረት ሁሉንም ነገር የምናይበት መነጽር መሆን አለበት። ወደ ውስጣችን የምንቀበለውንና ወደ ውጭ የምንሰጠውን ሁሉ የምናጣራበት ማጣሪያ መሆን አለበት። ዛሬ የእግዚአብሔር ምሕረት እጅግ ያስፈልጋል፤ መለኮታዊ የሆነው እርሱ ይህን ውድ ስጦታ በብዛት ለመስጠት እንደሚሻም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ምሕረት ምንድን ነው? በይበልጥ ለይተን ስንጠይቅ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ምንድን ነው? የእግዚአብሔር ምሕረት በሕይወታችን ውስጥ ሕያው ሆነው የሚሠሩ የእግዚአብሔር ጸጋና ፍቅር ነው። እግዚአብሔር በውስጣችን፣ በእኛ ላይና በእኛ በኩል መሥራቱ ነው። እግዚአብሔር ሕይወታችንን በእጁ ይዞ እንዴት ማሰብና እንዴት መሥራት እንዳለብን ማስተማሩ ነው። የምንኖርበት ዓለም እብደት እንዳይቆጣጠረን፣ እግዚአብሔር እኛን የራሱ ማድረጉ ነው።

የእግዚአብሔር ምሕረት በደረቀና በተጠማ በረሃ መካከል ውኃው ፈጽሞ የማያልቅ ምንጭ ይመስላል። አወቅነውም አላወቅነውም፣ ሁላችንም የምንፈልገው የመታደስና የአዲስ ሕይወት ምንጭ ነው። ልባችን ከሁሉ በላይ የሚናፍቀው፣ ያለንንም ናፍቆት ሊያረካ የሚችለው ብቸኛው ነገር ነው።

የምንኖርበት ዓለም በማያቋርጥ ስሜት ቀስቃሽ ነገር፣ ደስታ፣ ውጣ ውረድና ምስጢራዊ ጉዳዮች እኛን ለማርካትና ለማጥገብ ይሞክራል። ዓለም ያለማቋረጥ ሐሰተኛ የደስታና የእርካታ ስሜት ያቀርብልናል። የእግዚአብሔርን ምሕረት ለማግኘት የመጀመሪያው እርምጃ ዓለምን በእውነተኛ መልኩ ማየት ነው። በዙሪያችን ያሉትን ውሸቶችና ማታለያዎች አይተን፣ ወደዚህ ለእርሱ ወደተፈጠርንለት የእውነትና የጸጋ ምንጭ ዓይኖቻችንን ማዞር ነው። ወደ እግዚአብሔር ምሕረት መመለስ ያስፈልገናል።

በደረቅ ስፍራ እንደሚፈልቅ የጸጋ ምንጭ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ከተሰወረ ምንጭ ይመነጫል፤ ሳይቋረጥ ይፈስሳል፣ ፈጽሞም አያልቅም፤ በሕይወት እርካታ ለማግኘት የሚያስፈልገንን ሁሉ ያስገኛል።  ወደ ውስጡ ዘልቀን እንድንገባና ጥልቀቱን እንድንደርስ እንደተጠራንበት ሰፊ ውቅያኖስ ነው።  ማብቂያ የለውም፣ መላ ማንነታችንንም ይሞላል።

ኢየሱስ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ሁልጊዜ ምሳሌዎችን ሰጥቶናል። ከመንገድ የወጣው ልጁ እስኪመለስ የሚጠብቀው አፍቃሪ አባት እርሱ ነው።  የጠፋችውን አንዲት በግ የሚፈልገው ቸር እረኛ እርሱ ነው።  በከባድ ችግር ውስጥ የነበረውን እንግዳ የተንከባከበው ቸር ሳምራዊ እርሱ ነው።

እርግጥ ነው፣ እነዚህ የምሕረቱንና የፍቅሩን ጥልቀት ፈጽሞ ሙሉ በሙሉ ሊያስረዱ አይችሉም። እያንዳንዱ ምስል ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ግል ልምዱና የሕይወት ታሪኩ የራሱን ትርጉም ያመጣለታል። እግዚአብሔር በቅርብ ዘመን ከሰጠን ስጦታዎች አንዷ እህት ማሪያ ፋውስቲና ኮቫልስካ ናት። ኦገስት 25፣ 1905 በፖላንድ ክራኮው ተወለደች፤ ኦክቶበር 5፣ 1938 ደግሞ በዚያው ከተማ በሠላሳ ሦስት ዓመቷ አረፈች። ገና በሃያ ዓመቷ በዋርሶ ወደሚገኘው የእመቤታችን የምሕረት እህቶች ማኅበር ገባች፤ በኋላም ወደ ፕዎትስክ፣ ከዚያም ወደ ቪልኒየስ ተዛወረች። የንስሐ አባቷን አባ ሚኻው ሶፖችኮን ያገኘችው በቪልኒየስ ነበር። እሳቸውም ከእግዚአብሔር ከተቀበለቻቸው ብዙ ምሥጢራዊ ጸጋዎች ጋር በተያያዘ እጅግ ረዷት። እህት ፋውስቲና ከኢየሱስ በየቀኑ የግል መገለጦችን የመቀበል ጸጋ ተሰጥቷት ነበር፤ በእነዚህም አማካይነት የመለኮታዊ ምሕረቱን ብዛት ገለጠላት።

በበላይ ኃላፊዋ፣ በአባ ሶፖችኮና በራሱ በኢየሱስ መመሪያ መሠረት፣ እነዚህን ምሥጢራዊ ተሞክሮዎቿን በማስታወሻ ትመዘግብ ነበር። ይህም ማስታወሻ ዛሬ የእግዚአብሔር ምሕረት በነፍሴ ውስጥ፦ የቅድስት ማሪያ ፋውስቲና ኮቫልስካ ማስታወሻ። በሚል ርዕስ ይታወቃል።

የዚህ መጽሐፍ ዓላማ የእርሷን ማስታወሻ ገጾች እያነበብን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመልእክቶቹ ላይ እንድናሰላስል ነው።  በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በማስታወሻ ላይ የሚቀርቡት ማሰላሰያዎች፣ አንባቢው ኢየሱስ ራሱ ለእኅት ፋውስቲና የገለጠላትን የእግዚአብሔር ምሕረት መልእክት በቀላሉ ማሰላሰል እንዲችል በሚረዳ መንገድ ተዘጋጅተዋል።

በኤፕሪል 30፣ 2000፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በእግዚአብሔር ምሕረት እሑድ፣ እኅት ፋውስቲናን በቅዱሳን ተርታ አስመዘገቡ።  በቅዱሳን ተርታ በመመዝገቧ፣ የቅድስት ፋውስቲና መልእክቶች የእግዚአብሔርን የበዛ ጸጋ እጅግ ወደምትፈልገው ዓለም መስፋፋታቸውን ቀጥለዋል።

በዲሴምበር 8፣ 2015፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም ልዩ የምሕረት ኢዮቤልዩ ጀመሩ።  ይህ መጽሐፍ የዚያ የምሕረት ዓመት ፍሬ ነው። ገጾቹን የሚያነብብ እያንዳንዱ ሰው በሚመጡት ዓመታት ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ይበልጥ በጥልቀት እንዲገባ ለመርዳት፣ በዚያ የኢዮቤልዩ ዓመት ተጻፈ።

ማውጫ

የዚህ መጽሐፍ አደረጃጀት

ለካህናት መግቢያ

ማሰላሰያዎች፦ 1-10


በኤሌክትሮኒክ መጽሐፍ & በለስላሳ ሽፋን በታተመ መጽሐፍ መልክም ይገኛል

የእግዚአብሔር ምሕረት

አማዞን – ባርንስ ኤንድ ኖብል – ጉግል ፕሌይ – አይቱንስ