አማርኛ

ለካህናት መግቢያ

የእግዚአብሔር ካህን ሆይ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ያለማቋረጥ በእርስዎ ሥጋ እንዲለብስ ተጠርተዋል። ይህን እንዴት ያደርጋሉ? ስለ ምሕረት መስበክና በድርጊትዎ መሐሪ ለመሆን መጣር ብቻ በቂ ነውን? አይደለም፤ አንድ ካህን ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም ሊያቀርበው የሚገባው ምሕረት ከዚህ እጅግ የላቀ ነው።

ሊያቀርቡት የሚችሉት መሠረታዊ የምሕረት ተግባር፣ የተወጋውና የቆሰለው የክርስቶስ ልብ ለመሆን በነፃ ፈቃድዎ መምረጥ ነው። የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራዊ ሕይወት ደምና ውኃ የሚፈስሰው ከልቡ ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን የማንጻትና የመቀደስ ጨረሮች በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ላይ የሚያበራው ይህ የቆሰለ ልብ ነው።

እርስዎም ራስዎ በመወጋት፣ የዚህ ፍሰት ምንጭ እንዲሆኑ በልዩ ሁኔታ ተጠርተዋል። እግዚአብሔር ክህነትዎን እንደ ምሕረቱ መሣሪያ እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚፈልግ የሚያሳዩ አምስት ምክሮች እነሆ። እነዚህ አምስት ተግባራት የቤተ ክርስቲያንንና የዓለምን መንጻትና መቀደስ ያስገኛሉ። ከቆሰለው የክርስቶስ ልብ በሚፈስሰው ክህነታዊ አገልግሎት ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንዲካፈሉ ያስችሉዎታል።

1. መከራን በነፃ ፈቃድዎ ለመቀበል ይምረጡ

2. በሚቀበሉት መከራ ደስ ይበልዎ

3. መከራዎን ከኢየሱስ ጋር በአንድነት ለአብ ያቅርቡ

4. በመሥዋዕትዎ ዓለምን ያንጹ

5. በአገልግሎትዎ ቤተ ክርስቲያንን ይቀድሱ

መከራን በነፃ ፈቃድዎ ለመቀበል ይምረጡ

በክርስቶስ ልብ መከራ ለመካፈል በነፃ ፈቃድዎ ይምረጡ። እንደ ካህን፣ መከራ እንዲደርስብዎ በመፍቀድና ከዚያም በመቀበል ይህን በልዩ ሁኔታ ያደርጋሉ። በመጀመሪያ፣ የሚደርስብዎን ማንኛውንም ዓይነት በደል በነፃ ፈቃድዎ ለመቀበል ይምረጡ። ከዓለምም ሆነ ከራስዎ ሕዝብ የሚሰነዘርብዎን ማንኛውንም ፌዝ ይቀበሉ። ሌላ ሰው ሲነቅፍዎ ወይም ሲያወግዝዎ፣ አጸፋ አይመልሱ ወይም ራስዎን አይከላከሉ። ድርጊትዎን ለማስረዳትና ራስዎን ነፃ ለማውጣት አይሞክሩ፤ ለቁጣም እጅ አይስጡ። ይህን አያድርጉ። ይልቁንም፣ ማንኛውንም ውርደትና መከራ ከጌታ እንደመጣ ይቀበሉ፤ ምክንያቱም በኃጢአቶችዎ ሳቢያ ይህ ሁሉ ፈጽሞ ይገባዎታል። የመጀመሪያው እርምጃ ይህ ነው።

ሁለተኛ፣ ከተራ ነቀፋ ወይም ስደት እጅግ የጠለቀ ሥቃይ እንዲሰማዎ ለራስዎ ይፍቀዱ። በክርስቶስ መከራ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ የሚካፈልበት ልዩ ክህነታዊ ሥቃይ፣ ወንጌል ተቀባይነት በማጣቱ ምክንያት በክርስቶስ ልብ ያለው ሥቃይ እንዲሰማዎ ማድረግ ነው። ለእግዚአብሔር ሕዝብ ያለዎት ፍቅር፣ ኢየሱስ ያሳለፈውን እርስዎም እንዲያሳልፉ እስከሚያደርግ ድረስ ጠንካራና መላ ማንነትዎን የሚሞላ ይሁን። ወንጌል ተቀባይነት ሲያጣ የሚኖረውን ሥቃይ እንዲያሳልፉ ለራስዎ ይፍቀዱ። በእርግጥ፣ ወደ እርስዎ የሚሮጡ፣ ልብዎ ውስጥ ላለው ፍቅር ራሳቸውን ክፍት የሚያደርጉና ወንጌልን በደስታ የሚቀበሉ ብዙዎች አሉ። ይህ ለእርስዎ ታላቅ መጽናናት ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ የማያደርጉም ብዙዎች አሉ። ከራስዎ ልብና ከክህነታዊ አገልግሎትዎ ለሚያበራው የእግዚአብሔር ምሕረት ራሳቸውን ክፍት የማያደርጉ ብዙዎች አሉ። በክርስቶስ ልብ ፍቅር ከተካፈሉ፣ ለእነዚህ ነፍሳት እንዲህ ያለ ቅዱስ ናፍቆት እንዳለዎት ያውቃሉ። ይህ ናፍቆት እጅግ ጣፋጭና ጥልቅ የሆነ ሥቃይ ያስገኛል። ያንን ልዩ ክህነታዊ መከራ ይምረጡና በሙሉ ልብዎ ይቀበሉት።

 

በሚቀበሉት መከራ ደስ ይበልዎ

በክህነታዊ አገልግሎትዎ ውስጥ የሚያጋጥሙዎትን፣ በክርስቶስ ልብ ያሉትን መከራዎች በነፃ ፈቃድዎ ለመቀበል ከመረጡ በኋላ፣ አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄድ አለብዎት። በነፃ ፈቃድ መቀበሉ በታላቅ ደስታ ጭምር እንዲሆን ያድርጉ። እነዚህን መከራዎች መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በእነሱም ደስ ይበልዎ። በክህነታዊ አገልግሎትዎ ውስጥ፣ ታላቅም ሆነ ትንሽ፣ የክርስቶስ ልብ በሚወጋበት እያንዳንዱ ክስተት ደስ ይበልዎ። ልቡ የተሰማው ሥቃይ ለእርስዎም ስለተሰማዎ ደስ ይበልዎ፣ ጌታችንንም ያመስግኑ። እነዚህን መከራዎች በደስታ መቀበልዎ ኃይለኛ ምስክርነት ይሆናል፤ በተጨማሪም እንደ ካህን ሕይወትዎን መሥዋዕት አድርገው ወደ ፊት እንዲቀጥሉ ለእርስዎ በግል ብርታት ያስገኝልዎታል።

 

መከራዎን ከኢየሱስ ጋር በአንድነት ለአብ ያቅርቡ

በክርስቶስ ልብ ያሉትን መከራዎች በነፃ ፈቃድ መምረጥና በእነዚያ መከራዎች ደስ መሰኘት ብቻ በቂ አይደሉም። ቀጣዩ እርምጃ፣ በነፃ ፈቃድ የተመረጠውን ይህን መሥዋዕት፣ በመስቀል ላይ ከቀረበው የክርስቶስ መሥዋዕት ጋር በአንድነት ለአብ ማቅረብ ነው። ኢየሱስ መከራውን ለአብ ሲያቀርብ፣ ክህነቱን እጅግ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ይፈጽማል። እንደ ፍጹም ካህን ተልእኮውን እንዲፈጽም የሚያስችለው፣ ውርደቱንና ፍቅሩ ተቀባይነት በማጣቱ ምክንያት የደረሰበትን መከራ ማቅረቡ ነው። በተለይ ቅዱስ ቅዳሴን ሲያቀርቡ፣ በዚያ መሥዋዕት ከእርሱ ጋር ይተባበሩ። ይህን መሥዋዕት ዘወትርና በታሰበ ውሳኔ ያቅርቡ፤ ክህነትዎንም ፈጽሞ አዲስ በሆነ ደረጃ እየኖሩት እንደሆነ ይገነዘባሉ።

 

በመሥዋዕትዎ ዓለምን ያንጹ

ቤተ ክርስቲያን፣ ዓለምና የራሳችን ነፍስ መንጻትን እጅግ ይፈልጋሉ። መንጻት ወደ መቀደስ ይመራል፤ በነፃ ፈቃድ፣ በደስታ የሚያቀርቡት ክህነታዊ መሥዋዕትም ያነጻል። በዚህ ሦስት ገጽታ ባለው ተግባር፣ እርስዎ ይቀደሳሉ፣ ቤተ ክርስቲያንም ትቀደሳለች፣ ዓለምም የሚያስፈልገውን መንጻት እንዲቀበል ይጋበዛል።

የእግዚአብሔር ካህን ሆይ፣ ዓለምን በማንጻትና በመቀደስ የምትወጣውን ድርሻ አታቃልል። የእግዚአብሔር ምሕረት መሣሪያ የመሆን ይህ ድርሻ፣ ለመስበክና ምሥጢራትን ለማክበር ከተሰጠህ የጸጋ ስጦታ የሚበልጥ ነው፤ ሕይወትህን ለዓለም ድኅነት እያቀረብህ፣ ከክርስቶስ ጋር አንተም መሥዋዕት መሆን አለብህ። ከጌታችን ከቆሰለ ልብ የሚያበራው የእግዚአብሔር ምሕረት ያለማቋረጥ መፍሰሱን እንዲቀጥል የሚያደርግ መንገድ አድርገህ፣ ይህን የመሥዋዕትነት ድርሻህን ተቀበል።

 

በአገልግሎትህ ቤተ ክርስቲያንን ቀድስ

በመሠዊያው ላይ በምሥጢር ከሚገኝ የክርስቶስ መሥዋዕት ጋር በአንድነት፣ መከራን ሁሉ በየዕለቱ መቀበልን፣ በእርሱ መደሰትን እና ለአብ ማቅረብን ልማድ ካደረግህ በኋላ፣ በሌሎቹም የአገልግሎትህ ዘርፎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመቀደስ መጣር አለብህ። አገልግሎትህ ኃይል ያለውና በዓለማችን እጅግ የሚያስፈልግ ነው። ቁጥር የሌላቸው ነፍሳት ጌታችንን ለማግኘት ወደ አንተ ይመለከታሉ። በአገልግሎትህ ቸልተኛ አትሁን። በሁሉም ነገር ቅንዓት ያለህና በኃላፊነት የምትሠራ ሁን። በየዕለቱ ጸልይ፤ የጸሎትህም ፍሬ በክህነትህ አማካይነት የሚገለጠውን የክርስቶስን አገልግሎት እንዲመራ ፍቀድ። የእግዚአብሔርን ሕዝብ አስተምር፣ ቀድስ፣ እረኛም ሁንለት፤ በዚህም ልዩ ክብር አትታክት። ጌታ መርጦሃል፤ ከምታስበው በላይ በሆኑ መንገዶች ባንተ ሊሠራ ይፈልጋል።

ከክርስቶስ ልብ በሚፈሰው የእግዚአብሔር ምሕረት ይበልጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖርህ፣ ከታች የቀረበውን የካህን ጸሎት እንድትጸልይ ተጋብዘሃል፦

 

መከራንና ስደትን የተቀበልህ ውድ ጌታ ሆይ፣ ሥጋዬ የሚቀርብልኝን መከራ ለመቃወም ዘወትር ይፈተናል። ውድ ጌታ ሆይ፣ ከዚህ ሥቃይ ከመሸሽ ይልቅ፣ በነጻ ፈቃዴ ልመርጠው እፈልጋለሁ። አንተ ራስህ፣ «ሕይወቴን ከእኔ ማንም አይወስድብኝም፤ እኔ በነጻ ፈቃዴ አሳልፌ እሰጣታለሁ» ብለሃል። ጌታ ሆይ፣ አንተን በመምሰል፣ ዛሬ የሚሰጠኝን ሥቃይና መከራ ሁሉ እመርጣለሁ። ልቤን ደጋግመው የሚወጉት እነዚህ ሰይፎች በግድ የተጫኑብኝ እንዳይሆኑ ቆርጬ እወስናለሁ። ይልቁንም ስለ ጦሩና ያንን ጦር በልቤ ውስጥ ስለሚሰካው ወታደር አመሰግንሃለሁ። ይህ ስለሚያመጣው ሥቃይ አመሰግንሃለሁ። እነዚህን የማያቋርጡ ውጋቶች፣ በተለይም ወንጌልህ ተቀባይነት በማጣቱ የሚመጡትን፣ ለመቀበል ስለተሰጠኝ ክብርና ልዩ ዕድል አመሰግንሃለሁ። ጌታ ሆይ፣ እነዚህን የምቀበላቸው ብቻ ሳይሆን፣ እመርጣቸዋለሁ፤ በነጻ ፈቃዴም እመርጣቸዋለሁ።

ውድ የምሕረት ጌታ ሆይ፣ የሚሰማኝና አሁን በነጻ ፈቃዴ የምመርጠው ሥቃይ ደስታን ማፍራት አለበት። ስለዚህ፣ ጌታ ሆይ፣ በዚህ መከራ መደሰትንም እመርጣለሁ። በእያንዳንዱ የጦር ውጋት እደሰታለሁ። በእያንዳንዱ ኃይለኛና ሰርስሮ በሚገባ ሥቃይ እደሰታለሁ። ውድ ጌታ ሆይ፣ እንዲህ ያለ ሥቃይ እንዲሰማኝ ስለሰጠኸኝ ክብር ለዘላለም አመስጋኝ ነኝ። በውርደትህና በመከራህ እንድካፈል ስለፈቀድህልኝ አመሰግንሃለሁ። ሊዘባበቱብኝና ሊያንቁኝ፣ ሊንቁኝና ሊሳለቁብኝ ስለሚችሉ አመሰግንሃለሁ። ውድ ጌታ ሆይ፣ ከዚህም በበለጠ ጥልቀት፣ ለሕዝብህ ባለህ የሚነድ ፍቅር ምክንያት በተሰማህ መከራ መካፈል ስለምችል አመሰግንሃለሁ። ይህ ሥቃይ ከተራ ውርደት እጅግ የሚበልጥ ነው። ሕዝብህን ከመውደድና፣ ምሕረትህን ባለመቀበላቸው ምክንያት እንደ ካህን ልቀድሳቸው ካለመቻል የሚመጣው ሥቃይ፣ ከሁሉ የጠለቀ ሥቃይ ነው። ጌታ ሆይ፣ ለሕዝብህ ባለኝ ፍቅር ምክንያት ይህ እምቢታ እጅግ ስለሚያሠቃየኝ አመሰግንሃለሁ።

ሊቀ ካህናችን የሆንህ ውድ ጌታ ሆይ፣ አንተ ካህን ነህ፣ አንተም መሥዋዕት ነህ። እንደ ካህን የሥጋዊ ሕይወትህን መሥዋዕት ታቀርባለህ፤ ነገር ግን ከዚህም የሚበልጥ ነገር ታቀርባለህ። የውስጥ መከራዎችህንና ናፍቆቶችህን ሁሉ መሥዋዕትም ታቀርባለህ። ጌታ ሆይ፣ ይህን የክህነት መሥዋዕት ከአንተ ጋር ለአባትህ አቀርባለሁ። በመስቀል ላይ ካቀረብኸው ከራስህ መሥዋዕት ጋር በአንድነት አቀርበዋለሁ። ይህን ሥቃይ አሳልፈሃል፤ የፍቅርህ ፍሬ እንደሆነም ተደስተህበታል፤ ከዚያም ለአብ አቅርበኸዋል። ይህን የክህነት መሥዋዕት ከአንተ ጋር ላቅርብ።

ውድ የቅድስና ጌታ ሆይ፣ የመሥዋዕትህ ፍሬ የቤተ ክርስቲያንህ መንጻትና መቀደስ ነው። በመጀመሪያ መንጻት፣ ከዚያም መቀደስ ይመጣል። ከሁሉ ይልቅ የምጸልየው ለመንጻት ፍሬ ነው። እባክህ፣ የክህነት መሥዋዕቴን በማቅረቤ ቤተ ክርስቲያንህንና መላውን ዓለም አንጻ። በመጀመሪያ የራሴን ምስኪን ነፍስ አንጻ። ነገር ግን ከዚያ አልፈህ፣ ከቆሰለው ልብህ የሚፈሱት የምሕረትህ ጨረሮች ዓለምን እንዲነኩና እንዲቀድሱ እንድታፈስስ እለምንሃለሁ። ደምና ውሃ በእውነት እንዲፈልቁ፣ የልብህ ቁስል በስፋት ይከፈት። ውድ ጌታ ሆይ፣ ልቤ የቆሰለው ልብህ በሥጋ የሚገለጥበት ዘወትራዊ መገለጫ ይሁን። የተወጋውና ለመሥዋዕት የቀረበው ልቤ፣ በዚህ ዘመናችን ለቤተ ክርስቲያንና ለዓለም የምሕረት ምንጭ ይሁን። እባክህ፣ መፍለቅ ባለበት በአዲሱ የደምና የውሃ ምንጭ ካህናትን፣ ጳጳሳትን፣ ምእመናንንና መላውን ዓለማዊ ማኅበረሰብ አንጻ። ውድ ጌታ ሆይ፣ በዚህ ዓለም የመለኮታዊ ምሕረትህ መሣሪያ የመሆን ክብርና ልዩ ዕድል ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ማውጫ

ምዕራፍ አንድ – የመግቢያ ማሰላሰያዎች


በኤሌክትሮኒክ መጽሐፍ & በለስላሳ ሽፋን በታተመ መጽሐፍ መልክም ይገኛል

የእግዚአብሔር ምሕረት

አማዞን – ባርንስ ኤንድ ኖብል – ጉግል ፕሌይ – አይቱንስ