ሌሎች ስለ አንተ የሚያስቡት ጉዳይ አለውን? በሌላ አነጋገር፣ የሌሎች «አስተያየቶች» ሊያሳስቡህ ይገባልን? አዎንም፣ አይደለምም። አይደለም፤ ምክንያቱም ዋናው «አስተያየት» እውነት የሆነው ብቻ ነው፤ በዚህ መልኩ ስናየው፣ ሊያሳስቡን አይገባም። እውነትም በእግዚአብሔር ሐሳብ ያለው ነው። ያ እውነትም አስተያየት አይደለም፤ እውነት ነው። ስለዚህ፣ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ስለማያንጸባርቁ አስተያየቶች መጨነቅ የለብንም። ይሁን እንጂ፣ ለሌሎች ያለን ፍቅር ወደ እውነት እንዲደርሱ እንድንረዳቸው ሊገፋፋን ስለሚገባ፣ ከዚህ አንፃር የሌላው ሰው አስተያየት ሊያሳስበን ይገባል። አንዳንዶች ግትር ናቸው፤ ምንም ቢሆን፣ ከእውነት ይልቅ የራሳቸውን አስተያየት አጥብቀው ይይዛሉ። ይህን መቆጣጠር ከአቅማችን በላይ ነው። ሌሎች ግን ለመቀበል ዝግጁ ናቸው፤ የተከፈተ አእምሮና ልብ ካየንም፣ የተሳሳቱ አመለካከቶቻቸውን ትተው በእግዚአብሔር ሐሳብ ያለውን እንዲቀበሉ ለመርዳት፣ እግዚአብሔር በሚፈልገው በማንኛውም መንገድ ሊጠቀምብን ዝግጁ ልንሆን ይገባል (ማስታወሻ #763 ተመልከት)።
በተለይ፣ ሰዎች ስለ አንተ ምን እንደሚያስቡ ወይም እንደሚናገሩ ከልክ በላይ የመጨነቅ ዝንባሌህን አሰላስል። ይህ ጎጂ በሆነ መንገድ ተጽዕኖ እንዲያደርግብህ ትፈቅዳለህን? የራስህን ምርጫዎችና በሕይወትህ ትኩረት የምትሰጠውን ነገር እንዲወስን ትፈቅዳለህን? ዛሬ፣ ዋናው ነገር እውነት ብቻ መሆኑን ራስህን አስታውስ። በእግዚአብሔር ሐሳብ ያለው ምንድን ነው? ሊያሳስብህ የሚገባው ይህ ነው። ለዚያ እውነት ያለህን ቁርጠኝነት አድስ፤ እጅግ ታላቅ ነፃነትም ታገኛለህ።
ጌታ ሆይ፣ የእውነት ሁሉ አንድና ብቸኛ ምንጭ ወደሆንኸው ወደ አንተ እመለሳለሁ። በሐሳብህ ያለውን ብቻ ለማወቅና ለማመን እሻለሁ። ከዓለም አስተያየቶች ሁሉ ይልቅ ይህን እውነት እመርጣለሁ፤ አንተ የምትገልጠውን ብቻ ለመቀበል በመሻት፣ የራሴን አስተያየቶች ለመተው እመርጣለሁ። ሁልጊዜ በእውነት እንድኖር ጸጋህን ስጠኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።





