ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት፤ በሚሃይ ሙንካቺ የተሣለ
ለእግዚአብሔር ይበልጥ ዋጋ ያለው የትኛው ነው? ለማድረግ በምትነሣበት ነገር ሁሉ ስኬታማ መሆን፣ ወይስ የሕይወትን መከራ ሁሉ በትዕግሥትና በሰላም መቋቋም? ብዙዎች ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሊቸገሩና ሁለቱንም ለመምረጥ ሊፈልጉ ይችላሉ። በእርግጥ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ከእኛ የሚፈልገውን ሁሉ ለመፈጸም ብንነሣ፣ ይህ ለእግዚአብሔር መንግሥት ትልቅ ዋጋ እንደሚኖረው በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚጠራን፣ ችግር በሚታይበት ትግል መካከል ትዕግሥትንና ሰላምን አጥብቀን እንድንይዝ ቢሆንስ? ይህ ትልቅ ዋጋ አለውን? አዎን፣ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ አለው፤ ምክንያቱም በትዕግሥት በመጽናት እያደግን በምንሄድበት በዚህ ሂደት፣ በእውነት ቅዱሳን እንድንሆን እንደረጋለን (ማስታወሻ #86 ተመልከት)።
በየቀኑ ከሁሉ በላይ የሚከብድህ ምንድን ነው? ከሁሉ በላይ ትዕግሥትህን የሚፈትነው ምንድን ነው? ይህን ፈተና በሕይወትህ ደስታና እርካታ እንዳታገኝ የሚከለክል «እንቅፋት» አድርገህ ትመለከተዋለህ? እንዲህ ከሆነ፣ ከሌላ አቅጣጫ ለማየት ሞክር። ማንኛውንም ችግር በበጎ ምግባር፣ በተለይም በትዕግሥት ለማደግ እንደሚሰጥህ አጋጣሚ ለማየት ሞክር። በዚህ በጎ ምግባር ማደግ የክርስቶስን ልብ ያስደስታል፤ ለመንግሥቱም እጅግ ከፍተኛ ዋጋ አለው።
ጌታ ሆይ፣ ከሁሉ በላይ የሚከብዱኝን ነገሮች ለአንተ አስረክባለሁ። ስለ እነርሱ አመሰግንሃለሁ፤ ከማንኛውም ነገር በላይ በቅድስና እንዳድግ የሚረዱኝ እነርሱ እንደሆኑም አምናለሁ። በተለይም (ማንኛውንም የግል ችግርህን ጥቀስ) ለአንተ አቀርባለሁ። ጌታ ሆይ፣ ለአንተ እንደማቀርበው መሥዋዕት ተቀበለው፤ ወደ ፍቅርና ምሕረት እንድለውጠውም ጸጋህን ስጠኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።




