ምስሉ በ ሌሮይ ስካልስታድ ከ ፒክሳቤይ
የሌሎችን ስሜት በእውነትና ከልብ የመረዳትና የመጋራት እጥረት፣ የሆነ የሥነ ልቦና፣ የስሜት፣ እንዲያውም የመንፈሳዊ መታወክ ግልጽ ምልክት ነው። ይህ የተጠቀሰው ተቃራኒውም እውነት ስለሆነ ነው። የሌሎችን ስሜት በእውነትና ከልብ መረዳትና መጋራት፣ አንድ ሰው በሥነ ልቦና፣ በስሜትና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ጤናማ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው። የሌሎችን ስሜት መረዳትና መጋራት ማለት የሌላውን ሰው ሁኔታ ማስተዋል ማለት ነው። አንድ ሰው ሲሠቃይ ወይም ሲደሰት ይሰማሃል። ከዚህም በላይ፣ የሚሰማው ሥቃይ ይሰማሃል፣ የሚያገኘውንም ደስታ ትጋራለህ። ይህ ከእግዚአብሔር ምሕረት የሚፈስስ፣ በልብህ የሚከናወን የምሕረት ተግባር ነው። (ማስታወሻ #1039 ተመልከት)።
ዛሬ የሌሎችን ስሜት ስለ መረዳትህና ስለ መጋራትህ፣ ወይም ይህ ስለ መጉደሉ አሰላስል። የሌላ ሰው ደስታ ወይም ሥቃይ ሲያጋጥምህ፣ በአሳብህ፣ በልብህና በስሜትህ ውስጥ ምን ይከሰታል? ግድ ሳይሰጥህና ሳትቀርበው ዝም ብለህ ታልፈዋለህ? ወይስ ሰውነቱን ታያለህ፣ ክብሩን ትገነዘባለህ፣ በእንክብካቤ፣ በርኅራኄና በአክብሮትም ትይዘዋለህ? የሌሎችን ስሜት መረዳትና መጋራት በመጨረሻ የሚመለከተው የእያንዳንዱን ሰው ክብርና ያንን ክብር በአሳባችን፣ በስሜታችን፣ በቃላችንና በተግባራችን የመቀበል ችሎታችንን ነው። ዛሬ የሌሎችን ስሜት ምን ያህል እንደምትረዳና እንደምትጋራ በቅንነት ለማየት ሞክር፤ በዚህ ረገድ ያለብህ ጉድለት ካስገረመህም፣ ምክንያቱን በጥልቀት መርምር። ይህን ጉድለት ለማመን አትፍራ፣ መፍትሔውንም ለመፈለግ አትፍራ። ነገር ግን ስለ ሌሎች በጥልቅ የሚያስብ፣ በርኅራኄ የተሞላ ልብ እንደ በረከት እንደተሰጠህ ካየህ፣ ልብህ በእግዚአብሔር ምሕረት እየተካፈለና ያንንም ለሌሎች እያካፈለ ስለሆነ ደስ ይበልህ።
ጌታ ሆይ፣ ልቤ የመሐሪ ልብህ መሣሪያ እንዲሆን እጸልያለሁ። ከልብህ የሚፈስሱት የሌሎችን ስሜት የመረዳትና የመጋራት ችሎታ እና ርኅራኄ በጎደሉኝ በማናቸውም መንገዶች ፈውስን ስጠኝ። በምሕረትህም በመካፈሌ፣ የሌሎችን ትግሎችና ደስታዎች እንድጋራ በተባረኩሁባቸው መንገዶች ሁሉ አመሰግንሃለሁ። ጌታ ሆይ፣ የልቤ ጥልቅ ምኞት ልቤ እንደ ልብህ እንዲሆን በሕይወትህና በፍቅርህ መካፈል ነው። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።




