ቪዲዮ
ከሌላ ሰው ጋር ያለን ወዳጅነት የእግዚአብሔር ምሕረት ከሚፈስባቸው ኃይለኛ መንገዶች አንዱ ነው። ሆኖም ወዳጅነት በተለያዩ ደረጃዎች ሊኖር ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ትስስር ጥልቀት በሌላቸውና እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ይመሠረታል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ በጌታችን ውስጥ ጥልቅ መሠረት ይኖረዋል። የጥልቅ መንፈሳዊ ወዳጅነት ምልክት እርስ በእርስ መጸላለይ ነው። በእምነት የተሞላ ወዳጅ ከተባረክህ፣ እርስ በእርስ ለመጸላለይ በምታደርጉት ቁርጥ ውሳኔ ያንን ወዳጅነት አጽናው፣ ይበልጥም አጠናክረው። ሕይወታችሁንና ፍላጎቶቻችሁን እርስ በእርስ ተካፈሉ፤ ስለእነዚህም ፍላጎቶች ለመጸለይ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እርስ በእርስ በመጸላለይ የእግዚአብሔር ምሕረት በእያንዳንዳችሁ ሕይወት ውስጥ እንደሚፈስስና የእርስ በእርስ ትስስራችሁም በጌታ ውስጥ ይበልጥ እንደሚጠናከር ትገነዘባላችሁ። ይህ የእግዚአብሔር ምሕረት በረከት እንዲሁም ያ ምሕረት ያለማቋረጥ የሚፈስበት ምንጭ ነው (ተመልከት፦ ማስታወሻ #1171)።
ስላሉህ ወዳጅነቶች አሰላስል። የእያንዳንዱ ወዳጅነት መሠረት ምንድን ነው? ምናልባት እያንዳንዱ የተለየ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ቀላል ትውውቆች ይሆናሉ። ሌሎቹ ደግሞ ይበልጥ ጥልቅ በሆነ አንድ የሚያደርግ ትስስር ላይ የተመሠረቱ ይሆናሉ። ዛሬ በተለይ ሁለታችሁም ለእግዚአብሔር ባላችሁ ፍቅር ላይ ስለተመሠረቱ ወዳጅነቶች ለማሰላሰል ጊዜ ውሰድ። እንዲህ ያለ ወዳጅነት ከተባረክህ፣ በጋራ በመጸለይ ይበልጥ ለማጠናከር ጣር። ወዳጅህ ከሁሉ በላይ ስለሚያስፈልገው ነገር አሰላስል፤ ለዚህም ጉዳይ ለመጸለይ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። አንተም ፍላጎትህን ለወዳጅህ አካፍለው። ይህ እርስ በእርስ መጸላለይ የእግዚአብሔር ምሕረት የሚፈስበት ኃይለኛ ምንጭ ይሆናል።
ጌታ ሆይ፣ ዛሬ በተለይ ስላሉኝ ወዳጅነቶች አመሰግንሃለሁ። ወዳጆቼን ለአንተ አቀርባለሁ፤ የበዛ ጸጋም እንድታፈስስላቸው እለምንሃለሁ። ጌታ ሆይ፣ በተለይ በወዳጄ ሕይወት ውስጥ ያለውን ይህን ፍላጎት ለአንተ አቀርባለሁ (አንድ ፍላጎት ጥቀስ)። ውድ ጌታ ሆይ፣ ለእያንዳንዳችን ስላለህ የማይለወጥ ፍቅርና በሕይወታችን ውስጥ አንተ ራስህ ስለሰጠኸን ፍጹም የወዳጅነት ስጦታ አመሰግንሃለሁ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
ኦገስት 13 – ሰማዕታቱ ቅዱሳን፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጶንጥያኖስ እና ካህኑ ሂጶሊጦስ





