ክርስቶስ ስለ ኢየሩሳሌም ሲያለቅስ፣ በአሪ ሼፈር የተሣለ
ስለ እግዚአብሔር ፍትሕም ሆነ ስለ ምሕረቱ መናገር ተገቢ ነው። እነሱም እርስ በርሳቸው አይቃረኑም። እግዚአብሔርን ለማገልገል እምቢ ባሉት መላእክት ላይ ፍትሑ እንደተፈጸመ ሁሉ፣ ንስሐ ለመግባት እምቢ በሚሉትም ላይ ይፈጸማል። ነገር ግን ለአሁኑ፣ እግዚአብሔር መሐሪ ነው ማለት ይበልጥ ተገቢ ነው። እንዲያውም፣ እግዚአብሔር ፍትሐዊ ብቻ እንደሆነና ያለማቋረጥ ፍርዱን በእኛ ላይ እንደሚያወርድ በሚል ሐሳብ እንድንዋጥ ክፉው እጅግ ይፈልጋል። ይህን ሐሳብ ስንቀበል፣ ምሕረቱን ለመቀበል ፈቃደኞች እስከሆንን ድረስ እግዚአብሔር የፍትሑን ቅጣት እንደማያወርድብን መረዳት ይከብደናል። ምሕረቱን ፈልግ፣ በእርሱ እመን፣ ወደ እርሱም ሩጥ። ለአፍታ እንኳ አትጠራጠርበት። እግዚአብሔር ምሕረቱን ቀንና ሌሊት እንደሚሰጥህ፣ በብዛት ከማፍሰስም እንደማይታክት ዕወቅ። ፍትሑን ስታስብ ፍርሃት ሲያጋጥምህ፣ ዓይኖችህን ወደ ምሕረቱ አቅና፤ ከልቡ በሚፈነጥቁት ጨረሮች እየተሞላህ ከኃጢአት ሁሉ በቀላሉ መመለስ ትችላለህ (ማስታወሻ #1338 ተመልከት)።
ከእነዚህ ሁለት የእግዚአብሔር ገጽታዎች የትኛውን ይበልጥ ታሰላስላለህ? የእግዚአብሔር ፍትሕ ያስፈራሃል? ወይስ ምሕረቱ ያጽናናሃል? ሁለቱም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም አንዱን ስናስብ ሌላውን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። የእግዚአብሔርን ምሕረት ያለ አንዳች ጥንቃቄ እንደምናገኝ በድፍረት መተማመን የለብንም፤ ምሕረቱንም ወዲያውኑ ሳናስታውስ በፍትሑ ላይ ብቻ ሐሳባችንን ማሳረፍ የለብንም። ዛሬ ከሁሉ በላይ ምሕረቱን አሰላስል፤ ፍትሑንም መፍራት አያስፈልግህም። ልብህ ፍቅሩን እንዲያጣጥም ፍቀድለት፤ በሙሉ እምነትና መተማመንም ወደ እርሱ ተመለስ።
ጌታ ሆይ፣ አንተ ፍትሐዊ እንደሆንህ፣ ወደ ምሕረትህም ካልተመለስሁ ፍትሕህን በእኔ ላይ እንደምትፈጽም ዐውቃለሁ። ስለዚህ ወደ ምሕረትህ እመለሳለሁ። በፍጹም ልቤም እሻዋለሁ። ጌታ ሆይ፣ እወድሃለሁ፤ ይበልጥም ልወድህ እመኛለሁ። ዓይኖቼን ወደሚያበራው ልብህ እንዳቀና፣ ልትሰጠኝ የምትፈልገውንም ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ እንድሆን ጸጋህን ስጠኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
ለሊዝየዋ ቅድስት ቴሬዝ — ለትንሿ አበባ — የሚቀርብ የዘጠኝ ቀን ጸሎት
ሦስተኛ ቀን- ሴፕቴምበር 24




